Abstract:
ይህ ጥናት ዋና ትኩረቱን ያደረገው በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል “በኢሉ አባቦር ዞን ዶረኒ
ወረዳ በኦሮሞ ማህበረሰብ ድንግልናቸውን ጠብቀው ለትዳር ለበቁ ሴቶች የሚደረግ
ሥርዓት ትንተና” በሚል ርዕስ የተካሄደ ነው። ጥናቱ በማህበረሰቡ ከሚከወኑ የሰርግ
ሥርዓቶች መካከል በነቀታ (Naqataa) የጋብቻ አይነት ድንግልናቸውን ጠብቀው ለጋብቻ
ለበቁ ሴቶች ስለሚደረገው ሥርዓት፣ ለማህበረሰቡ የሚሰጠዉን ማህበራዊና ስነልቦናዊ ፋይዳ
እንዲሁም ሥርዓቱ አሁን ስላለበት ሁኔታ ለማሳየትና ሰንዶ ለማኖር አልሞ የተነሳ ነው።
አጥኚዋ የጥናቱን አላማዎች ከግብ ለማድረስ ገላጭ የምርምር ዜዴን ተጠቅማለች። በጥናቱ
በወረዳው ካሉ አስራ ሁለት ቀበሌዎች መካከል በአላማ ተኮር የንሞና ዘዴ በተመረጡ
አራት ቀበሌዎች ላይ መረጃዎች ተሰብስበዋል። መረጃ አቀባዮቹ ታላሚ የንሞና ዘዴና በጓድ
ጥቆማ የተመረጡ ሲሆን የአካባቢውን ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ የባህሉ ባለቤቶችና
በሥርዓቱ ጋብቻቸውን የመሰረቱ ናቸው። ቃለ መጠየቅ፣ ቡድን ተኮር ውይይት እንዲሁም
ሰነድ ፍተሻ የመረጃ መሰብሰቢያ ዜዴዎችን በመጠቀም የጥናቱ መረጃዎች ተሰብስበዋል።
መረጃዎቹም እንዳስፈላጊነታቸውና እንደ መረጃ ሰጪዎች ፍቃደኝነት በቪድዮ፣ በፎቶ
ግራፍ፣ በመቅረጸ ድምጽና በማስታዎሻ ደብተር ተሰንደዋል። የተሰበሰቡ መረጃዎችም
በኮድ በመከፋፈል ተደራጅተው በአይነታዊ የመረጃ መተንተኛ ዘዴ ተተንትነው
ቀርበዋል።
የጥናቱ ወጤት እንደሚያመለክተው በኢሉ አባቦር ዞን ዶረኒ ወረዳ የኦሮሞ ማህበረሰብ
የተለያዩ የጋብቻ አይነቶች ያሉት ሲሆን ድንግልናቸውን ጠብቀው ለትዳር ለበቁ ሴቶች
የሚደረገው ሥርዓት በነቀታ (Naqata) የጋብቻ አይነት ይከወናል። በሥርዓቱ ከትዳር
መረጣ ተጋቢዎች ጋብቻ እስከሚመሰርቱበት ቀን ድረስ በተለያዩ ሂደቶች ውስጥ ይታለፋል።
ማህበረሰቡም ድንግልናቸውን ጠብቀው ለትዳር ለበቁ ሴቶች የሙሽራዋን ክብርና ጨዋነት
ለማሳየት ሲሉ የተለያዩ ክወኔዎችና ተግባራት እንደነበራቸው የጥናቱ ወጤት ያሳያል።
በወረዳው የሚኖረው የኦሮሞ ማህበረሰብ ልጃገረዶች የከንፈር ወዳጅ እንዲኖራቸው
እንዲሁም በአብዛኛው በሌሊት ጊዜ በሚከወን ባህላዊ ጭፈራ ላይ መሳተፍ
ይፈቀድላቸዋል። በመሆኑም ወጣቶቹ በባህላዊ ጭፈራው በሌሊት ሜዳ ላይ ከከንፈር
VII
ወዳጆቻቸው ጋር አብሮ የመጨፈር፣ የመሳሳም እና የመተቃቀፍ መብት አላቸው።
በተቃራኒው ከዚህ ጋር ተያየዞ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ተቋቁመው ድንግልናቸውን
ጠብቀው ለትዳር መብቃት እንደሚጠበቅባቸው በጥናቱ ተረጋግጧል።
ድንግልናን ጠብቆ ለትዳር መብቃትን አስመልክቶ የሚደረገው ሥርዓት ለማህበረሰቡ
የሚያስገኘውን ጠቀሜታ አስመልክቶ በነቀታ የጋብቻ አይነት በተጋቢዎች ቤተሰብ ደረጃ
በከፍተኛ መጠናናት የሚመሰርት በመሆኑ ትስስሩ ከተጋቢዎች አልፎ ጠንካራ ማህበራዊ
ግንኙነትን ይፈጥራል። ከስነልቦና አኳያም ለተጋቢዎቹም ሆነ ለተጋቢዎቹ ቤተሰቦች
መረጋጋትን፣ ክብርን፣ ደስታን እንዲሁም ፍቺን ከመቀነስ አንጻር ጠቀሚታው የጎላ ሲሆን
በግብረ ስጋ ግንኙነት አማካኝነት ከሚተላለፉ በሽታዎችና ከስነ ተዋልዶ ጤና አንጻርም
ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል። ነገር ግን ባህላዊ ሥርዓቱ በተለያዩ
ምክንያቶች ማለትም በቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ በሀይማኖታዊ ተጽኖ፣ በዘመናዊነት
አስተሳሰብ መስፋፋት እና በዘመናዊ አስተዳደር ህጎች ሳቢያ በአሁን ወቅት ሙሉ በሙሉ
እንደጠፋ ማረጋገጥ ተችሏል።
ከላይ የቀረቡትን የጥናቱን ግኝቶች መሰረት በማድረግ ድንግልናቸው ጠብቀው ለትዳር
ለበቁ ሴቶች የሚደረገው ሥርዓት ለተጋቢዎች ሆነ ለተጋቢዎች ቤተሰብ በሚያስገኘው
ስነልቦናዊ ፋይዳ የትዳር ፍቺን ከመቀነስ አኳያ አስተዋጾ የጎላ በመሆኑ ጠቃሚ ባህሉ
የሚያገግመበት ሁኔታ ቢፈለግ መልካም ይሆናል፤ እንዲሁም ባህላዊ ሥርዓቱ ከመጥፋቱም
ባሻገር ስለባህሉ ጠንቅቀው የሚያውቁ የባህሉ ባለቤቶች በእድሜ መግፋት ምክንያት
ከማለፋቸው በፊት መረጃው ተሰንዶ ለተተኪው ትውልድ የሚተላለፍበት መንገድ ቢፈልግ
፤ በተጨማሪም በወረዳው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተቀርጸው የተቀመጡትን ባህላዊ እሴቶች
በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ወደ ህዝብ የሚደርሱበት ሁኔታዎች ቢመቻች ጠቃሚ ይሆናል።
በመጨረሻም በወረዳው እየከሰሙ ያሉ ፎክሎራዊ እሴቶች ሙሉ በሙሉ ከመጥፋታቸው
በፊት ተቀርጸው የሚቀመጡበት ሁኔታ ቢፈጠር እና ሌሎች ተመራማሪዎች ይህንን ጥናት
መነሻ በማድረግ በወረዳው የሚታወቁ የጋብቻ አይነቶችን በንጽጽር እንዲሁም እያንዳንዱ
ባህላዊ ሥርዓቶችን ከፎክሎራዊ ጽንሰ ሃሳብ አንጻር ቢያጠኑ መልካም ነው በማለት አጥኚዋ
አስተያየቷን አስቀምጣለች።