Abstract:
ይህ ጥናት በደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ እምቢታ የተሰኘው ታሪካዊ ልቦለድና በአንዷለም
አባተመኤኒት በተሰኘ ልቦለድ ላይ የተካሄደ ነው፡፡ ጥናቱ በአራት ክፍሎች የተደራጀ
ሲሆን አካሄዱ ደግሞ በሁለቱም ልቦለዶች ውስጥ የተነሱ ፎክሎራዊ ጉዳዮችን በመለየት፤
በትዕምርትነት የተገለፁትን ከልቦለዶቹ አዉድ በመነሳ በመተርጎም ፎክሎራዊ ጉዳዮቹ
ለልቦለዱ መሳካት ያበረከቱትን ፋይዳ በመተንተን ነዉ፡፡ ጥናቱ የተከተለው አይነታዊ
ምርምር ዘዴን ሲሆን ዓላማ ተኮር የንሞና ዘዴ ተግባር ላይ ዉሏል፡፡ በጥናቱ
የስነጽሁፍንና ፎክሎርን መላመድ (ተዛምዶ) ለማሳየት የIntertextuality ንድፈ ሃሳብ
በመተንተኛነት አገልግሎት ላይ የዋለ ሲሆን በዋናነት ያተኮረው በልቦለዶቹ ውስጥ በተነሱ
የስነቃል ምድቦች መካከል ምርቃት ፣ እርግማን ፣ መሃላ ፣ ምሳሌያዊና ፈሊጣዊ አነጋገሮች
በሁለቱም ስራዎች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በእምቢታ ታሪካዊ ልቦለድ ውስጥ የውዳሴ ቃል
ግጥሞች በመኤኒት ልቦለድ ውስጥ ደግሞ ፉከራዎች ይገኙበታል፡፡ ሃገረሰባዊ ልማዶችን
በተመለከተ በሁለቱም ሥነ-ፅሁፋዊ ስራዎች ውስጥ ሰፊውን ቦታ የያዙ ሲሆን ክብረ
በዓላትና ሃገረሰባዊ ስያሜዎችም ተወስተዋል፡፡ቁሳዊ ባህሎችንበሚመለከቱ ባህላዊ
አልባሳቶች፤ ጌጣጌጦች፤ ሃገረሰባዊ ምግብና መጠጦችና ባህላዊ ቦታዎች በሁለቱም ስራዎች
ውስጥ የተገኙ ሲሆን “በእምቢታ ታሪካዊ ልቦለድ ውስጥ ደግሞ ሃገረሰባዊ ትዕምርቶች
ተገኝተዋል፡፡ በዚሁ መሰረት በሁለቱም ስራዎች ውስጥ የተለዩት እነዚህ የፎክሎራዊ
ጉዳዮች ፋይዳ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ በልቦለዶቹ ውስጥ የተሳሉትን ገፀባህሪያት
ማንነት በቀላሉ ለመረዳት፤ በዘመኑ የነበረውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ አጠቃላይ
መንፈስ ለማሳየት፤ የልቦለድ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግጭት ለማክረርና በተቃራኒዉ
ግጭቱን በማብረድ አንባቢን እፎይታ ለመስጠት፤ ጭብጡን ለመንገርና ለማጉላት፤
የልቦለዱን ትልም ለማዋቀር፤ በንግር ቴክኒክ ታሪኩ በአንባቢያን እንዲገመት በማድረግ
ረገድ ኪናዊ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን የጥናቱ ውጤት ያመላክታል፡፡ እነዚህን ፋይዳዎች
መነሻ በማድረግም ደራሲያን በድርሰት ስራዎቻቸው ውስጥ ፎክሎራዊ ጉዳዮችን
አገልግሎት (ጥቅም) ላይ ማዋል ቢችሉ ለሥነ-ፅሁፍ እድገትም ሆነ ለፎክሎር በዘላቂነት
ተቀርሶ መቆየት ከፍተኛ ጠቀሜታ ሊኖረው መቻሉን በጥናቱ ይሁንታ ክፍል ውስጥ
ቀርቧል፡፡