Abstract:
የዚህ ጥናታዊ ፅሁፍ ዋነኛ አላማ በኢሉአባቦር ዞን፣ በቡሬ ወረዳ በተመረጡ ሁለተኛ ደረጃና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ኢ-አፍ ፈት መምህራን አፍ ፈት ያልሆኑበትን የአማርኛ ቋንቋ ሲያስተምሩ የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ምን ምን እንደሆኑ መፈተሽ ነው፡፡ የጥናቱን አላማ ከግብ ለማድረስ የተመረጠው የጥናት ንድፍ ገላጭ የምርምር ስልት ሲሆን በተጨማሪም ቅይጥ (አይነታዊ እና መጠናዊ) የምርምር ዘዴን ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ይህን ጥናት ለማካሄድ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በኢሉባቡር ዞን ካሉ አስራ አራት ወረዳዎች መካከል የቡሬ ወረዳ የተመረጠዉ አመቺ የንሞና ዘዴን በመጠቀም ነው፡፡ ቀጥሎም በአላማ ተኮር ናሙና ዘዴ የጥናቱ መረጃዎች በወረዳው በሚገኙ ከ5 - 8ኛ ክፍል የሚያስተምሩ አንደኛ ደረጃ እና ከ9 - 12ኛ ክፍል የሚያስተምሩ ሁለተኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ኢ-አፍ ፈት የአማርኛ ቋንቋ መምህራን ብቻ የጥናቱ ተተኳሪ ተደርገዋል፡፡ አጥኚዉ ለጥናቱ ግባኣት መረጃ ይሰጡኛል ብሎ ያመነባቸዉን ከ21 ትምህርት ቤቶች በአላማ ተኮር ንሞና ዘዴ የተመረጡ 42 ኢ-አፍ ፈት የአማርኛ ቋንቋ መምህራንን የጥናቱ ተሳታፊዎች አድርጓል፡፡ አጥኚው ለምርምሩ በመረጃ መሠብሰቢያ መሳሪያነት የተጠቀመባቸው 3 የመረጃ መሰብሰቢያዎች ሲሆኑ፤ እነሱም የክፍል ምልከታ፣ የጽሁፍ መጠይቅና ቃለ መጠይቅ ናቸው፡፡ በሦስቱ መረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች የተሰበሰቡት መረጃዎች እርስ በእርስ ተደጋጋፊ በሆነ መልኩ በቡሬ ወረዳ በሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ ኢ-አፍ ፈት የአማርኛ ቋንቋ መምህራን በመማር ማስተማር ሂደት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ጉልህነት ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ የጥናቱ ግኝቶች እንዳመለከቱት በምልከታ ከተጎበኙት ናሙና ትምህርት ቤቶች መካከል አብዛኛዎቹ ኢ-አፍ ፈት የአማርኛ ቋንቋ መምህራን የኢ-አፍ ፈትነት ተግዳሮቶች ጎልተው የሚታዩባቸው በመሆናቸው በመማር ማስተማሩ ሂደት የተቆጣጣሪነት፣ የአደራጅነት፣ የአነቃቂነት፣ የመረጃ ምንጭነትና የገምጋሚነት ሚናዎቻቸውን በአጥጋቢ ሁኔታ ተወጥተዋል ለማለት እንዳልተቻለ ፍተሻው አረጋግጧል፡፡ መረጃዎች እንዳመላከቱት ኢ-አፍ ፈት የአማርኛ ቋንቋ መምህራን በመማር ማስተማር ሂደት ከሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች መካከል ዋነኞቹ የአማርኛ ቋንቋ መሰረታዊ እውቀት ውሱንነት፣ በአማርኛ ቋንቋ መምህርነት የተመደቡ አንዳንድ ኢ-አፍ ፈት መምህራን የአማርኛ ቋንቋ መምህር እጥረት ክፍተትን ለመሙላት እንጂ በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ የሰለጠኑበት የትምህርት አይነት ባለመሆኑ የተነሳ እንደ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው አድርገው ለማስተማር በራስ መተማመን የሚጎድላቸው መሆኑ፣ የቋንቋውን መዋቅራዊ ስርዓት በትክክለኛው ቦታና ጊዜ ለመጠቀም የሚቸገሩ መምህራን መኖር እንዲሁም የተለያዩ የቋንቋውን ይዘቶችን ለምሳሌ ቃላት፣ ስዋስው ሲያተምሩ ወደ አፍ መፍቻ ቋንቋ መሳብ የመሳሰሉ ተግዳሮቶች ተጠቁመዋል፡፡ በቡሬ ወረዳ በሚገኙ በተለይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ኢ-አፍ ፈት መምህራን አማርኛ ቋንቋን በሚያስተምሩባቸው መማሪያ ክፍሎች ውስጥ በመማር ማስተማር ሂደት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመቀነስ ይረዳቸው ዘንድ የተለያዩ ስልቶችና ብልሃቶችን የመጠቀም ተነሳሽነት በጣም ውሱን መሆኑንና የማስተማሪያ ስልቶችና ብልሃቶች ግንዛቤና ልምድ እጥረት የሚታይባቸው መሆኑን ፍተሻው አረጋግጧል፡፡