Abstract:
ይህ ጥናት ዋና ዓላማው በቤንችኛ ቋንቋ አፍ-ፈት ተማሪዎች በአማርኛ ቋንቋ ድርሰት ሲጽፉ የሚፈጽሟቸው ስህተቶችና የስህተት ምንጮችን መመርመር ነው፡፡ ተጠኝ ተማሪዎች በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የተመረጠው የሚዛን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዘጠነኛ ክፍል በ2013 ዓ.ም ከሚማሩት በቤንችኛ ቋንቋ አፍ-ፈት ተማሪዎች ናቸው፡፡ በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት 64 ተማሪዎች ሲሆኑ የተመረጡትም በቀላል የእጣ ናሙና ዘዴ ነው፡፡ ለጥናቱ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት በተተኳሪ ተማሪዎች በሁለት ዙር 128 ድርሰቶችን እንዲጽፉ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሰረት ተማሪዎች ከፃፏቸው ድርሰቶች ውስጥ የፈፀሟቸው ስህተቶችን ለመለየት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በተማሪዎችና በመምህራን የሚሞሉ የጽሁፍ መጠይቆች ቀርቦላቸው የተሰጠው ግብረ መልስ በስራ ላይ ውለዋል፡፤ ከላይ በቀረበውን መረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች እና በተተኳሪ ተማሪዎችና መምህራን የተገኙትን ጽሁፎች መሰረት በማድረግ ለድርሰቱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመመለስ ተሞክሯል፡፡
ከተፃፈው ድርሰት ከተገኘው ውጤት መሰረት ዋና ዋና የስህተት አይነቶች በቅደም ተከተላቸው ሲገለፁ አንደኛ፣ የቋንቋ አጠቃቀም 2480 (105.07)፣ሁለተኛ የስርዓተ ነጥብ አጠቃቀም 1400 (57.83) እና መለየት ያልተቻሉ 270 (72) ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ አብይ የስህተት ምድብ ስር ዝርዝር የስህተት ምድቦችን ይዟል፡፡በድርሰቱ ውስጥ ከቀረቡት በቋንቋ አጠቃቀም የታዩ ስህተቶች የቃላት አጠቃቀም ፣ ድግግሞሽ እና የፊደላት (ሆሄያት) አፃፃፊ ተብለው በንኡሳን ክፍል የተመደቡ ሲሆን በስርዓተ ነጥብ አጠቃቀም ስር የተፈፀሙ ስህተቶች የአራት ነጥብ ፣ የነጠላ ሠረዝ አጠቃቀም፣ የትዕምርተ ጥቅስ አጠቃቀምና የድርብ ሰረዝ አጠቃቀም የተከሰቱ ንኡሳን ስህተቶች ተከፍለው ተፈትሸዋል፡፡ በመጨረሻም መለየት ያልተቻሉ ስህተቶች በተተኳሪ ተማሪዎች ድርሰት ውስጥ ታይተዋል፡፡ ለስተቶቹ ምንጭ ይሆናሉ ተብለው የታመኑባቸው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ተፅዕኖ፣ የውስጠ ቋንቋ ተፅዕኖ፣ የማስተማሪያ መሣሪያዎችና ዘዴዎች ድክመት በተጨማሪ ስነልቦናዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፤ በመጨረሻም ማጠቃለያና የተከሰቱ ስህተቶችን ለመቅረፍ ያስችላሉ ተብለው የታመነባቸውን የመፍትሄ ሀሳቦች ተጠቁሟል፡፡