Abstract:
ይህ ጥናት ከ2008-2013 ዓ.ም. የተዘፈኑ የተመረጡ የአማርኛ ፖለቲካዊ ዘፈኖች አንድምታ በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን ዋና ዓላማው የዘፈኖቹን አንድምታ መተንተን ነው፡፡ ንዑሳን ዓላማዎቹ ደግሞ የዘፈኖቹን የጋራ ጭብጥና አንድምታ ማብራራት፣ ዘፈኖቹ የወቅቱን ፖለቲካዊ ሁነትና ማህበረሰባዊ ስሜት እንዴት እንደገለፁት መመርመር፣ የዘፈኖቹን ማህበረ ፖለቲካዊ ፋይዳ መግለፅ የሚሉት ናቸው፡፡ ጥናቱ በገላጭ የምርምር አይነትና በአይነታዊ የመረጃ መተንተኛ ዘዴ የቀረበ ሲሆን የመተንተኛ ንድፈ ሀሳቡን የሀዲስ ታሪካዊ ንድፈ ንድፈ ሀሳብን (New historicism theory) እና አውዳዊ ንድፈ ሀሳብን (contextual approach) ተጠቅሞ መረጃዎቹን ተንትኗል፡፡ በዚህ መልኩ የተተነተኑት መረጃዎች የሚያሳዩትም ለጥናቱ በተመረጠውና እንደየወቅቱ ፖለቲካዊ ድባብ በሶስት ምድብ ተከፋፍሎ በቀረበው የጊዜ ክልል ውስጥ የተዘፈኑት ሁሉም ዘፈኖች አንድምታ በተለያየ መልኩ ትርጓሜ የሚሰጣቸው እንደሆነ ነው፡፡ በሁሉም ዘፈኖች ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች ከወቅቱ ፖለቲካዊ አውድ አንፃር በርካታ ፍቺዎችን የያዙና በዚያው ልክ ለማህበረ-ፖለቲካው ያበረከቱት ጠቀሜታ በተለያየ መልኩ የተገለጠ ነው፡፡ በጥናቱ እንደተረጋገጠው ዘፈኖቹ የማህበረሰብን ስሜት በመጋራት ለውጥ ሽቶ ሲወጣ ለማጠንከርና ትግሉ እንዳይቀለበስ፣ ተቃውሞና ትግሉ ለውጥ ሲያስገኝና ህዝብ ሲደሰት ያንኑ የማህበረሰብ ስሜት አጉልቶ ለማሰማት፣ ተስፋ ሰንቆ ተስፋውን ሳያገኝና እርካታ ሳይሰማው ሲቀር ተስፋ ያሳጣውን ጉዳይ በአንክሮ በመመልከት ዳግም ቅሬታን ለማስተጋባት ውለዋል፡፡ የዘፈኖቹ ዋናው ማህበረ-ፖለቲካዊ ተግባር የነበረውም ትችት፣ ተቃውሞና ውዳሴ ነው፡፡ ውዳሴው በጥናቱ በተለያየ መልኩ የታየ ሲሆን የመጋቢት 24/2010 ዓ.ም ለውጥን የተመለከተ ነው፡፡ ተቃውሞው ደግሞ ከመስከረም 2008 እስከ መጋቢት 24/2010 ዓ.ም እና ዳግም ከ20011- 2013 ዓ.ም ይታዩ የነበሩትን ዘረኝነትን፣ ኢ-ፍትሀዊነትን፣ የሰብአዊ መብት ጥሰትን፣ ሙስናን፣ የመሪዎችን ገደብ የሌለው የስልጣን ፍቅርን በመተቸት የተቃወሙ እንደሆኑ በጥናቱ መረዳት ተችሏል፡፡