Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና አላማ የአፋን ኦሮሞ አፈ-ፈት ተማሪዎች አማርኛን በሁለተኛ ቋንቋነት
ለመማር ያላቸውን ተነሳሽነትና የትምህርት ውጤት ተዛምዶ መፈተሸ ነው፡፡ ጥናቱ
የተካሄደው በጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳ ቢፍቱ ጊቤ ሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤት በ2015ዓ.ም በ10ኛ
ክፍል ተማሪዎች ላይ ነው፡፡ የተሰበሰበው መረጃም ከጥናቱ ዓላማና መሪ ጥያቄዎች አንጻር
በገላጭ ስታቲስቲክስ በመታገዝ ተብራርቱዋል፡፡ በመረጃው ትንተና መሠረት በተማሪዎቹ
አማርኛን በሁለተኛ ቋንቋነት የመማር ተነሳሽነት ጥሩ ደረጃ የታየ ሲሆን ነገር ግን የአማርኛ
ፈተና ውጤታቸው ከተነሳሽነታቸው ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ሆኖ ታይቱዋል፡፡ ከጥናቱ
ውጤትም በመነሳት አጥኚዋ የሚከተሉትን የአስተያየት ነጥቦች አስቀምጣለች፡፡ በክፍል
ውስጥ የቋንቋ መምህራን የተማሪዎች የመማር ተነሳሽነት መኖር ወይም አለመኖር
በትምህርት ውጤታቸው ላይ የበኩሉን ተጽእኖ እንደሚያሳድር በመገንዘብ፣ የቋንቋ
ትምህርቱን የተማሪዎችን ፍላጎትና ስሜት በሚያነሳሳ መልኩ ቢያቀርቡ፤ መምህራን
ከትምህርት አቀራረባቸውም በተጨማሪ የተማሪውን ተነሳሽነት ወደ ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ
ስልቶችን በመጠቀም የተማሪዎች የውጤት መሻሻል ላይ ቢሰሩ፤ የሰርዓተ ትምህርት
ቀራጮችና የትምህርት መሳሪያ አዘጋጆች በዝግጅታቸው ወቅት የሁለተኛ ቋንቋ ትምህርት
ተማሪዎችን የተነሳሽነት ሁኔታ ከግምት ቢያስገቡ፤ በአጠቃላይ ኢ-አፈፈት ተማሪዎች
የአማርኛ ቋንቋ የመማር ተነሳሽነታቸው የጎላ ሊሆን የሚችል ቢሆንም በውጤት ረገድ
ዝቅተኛ ሊሆኑ ስለሚችሉ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚሉት በአጥኚዋ የተቀመጡ የመፍትሄ
ሀሳቦች ናቸው፡፡