Abstract:
የዚህ ጥናት አቢይ ዓላማ ‹‹ግራኝነት በካፋ ብሔረሰብ ዘንድ ያለውን ማህበራዊ ፍልስፍና
(ትዕምርትነት) መተንተን›› ነው፡፡ የጥናቱ ዘዴ አይታዊ ሲሆን የመተንተኛ ስልቱ ደግሞ
ገላጭ ትዕምርታዊ ፍከራን የተከተለ ነው፡፡ በታላሚና በጠቋሚ ከተመረጡ መረጃ አቀባዮች
አስፈላጊውን መረጃ በቃለመጠይቅና በሰነድ ፍተሻ፤ መቅረፀ ድምፅና ማስታወሻ ደብተር
መረጃ መቅረጫ መሳሪያዎችን በመጠቀም መረጃው ተሰብስቧል፡፡ ጥናቱ በካፋ ብሔረሰብ
በቦንጋ ዙሪያ፣ በጠሎ እና ዴቻ ወረዳዎች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ የተሰራ ነው፡፡
ከመስክ የተሰበሰበው መረጃ ላይ በተደረገው ትንተናም መሰረት ግራኝነት የሰይጣንነት፣
የክፋት፣ የስግብግብነት ወይም የአልጠግብ ባይነት እንዲሁም በብሔረሰቡ ዘንድ
በሚታመኑ ሀገረሰባዊ ዕምነቶች አንፃር የእርኩስነት ትዕምርትነት ያለው መሆኑ
ተመላክቷል፡፡ ሚት ውስጥ ግራኝነት የሰይጣን፤ በተረት ውስጥ ግራ የስውር ተንኮል፣
በምሳሌያዊ አነጋገር ውስጥ የአቅመቢስነት ወይም የአለመታመንና የርኩስ ወይም የመናቅ
እንዲሁም በፈሊጣዊ አነጋገር ውስጥ ደግሞ በኢ-ፍትሃዊነት ትዕምርትነት መቅረቡ
ተገልጿል፤ ማህበረሰቡ ግራኝነትን በመጥፎ ተምሳሌትነት ወይም ትዕምርትነት እንዲወክል
ተፅዕኖ እንዲኖር በዋናነት ያስቻሉት ስነቃዊ እሴቶችና የሀገረሰባዊ ዕምነት አስተምህሮ
ተፅዕኖዎች እንደሆኑ፤ ህፃናት ግራኝ እንዳይሆኑ ጥብቅ ክትትልና ግራኝ ከሆኑ የከፋ
ቅጣት እስከማስከተል እንደሚደርስ፣ ቅጣቱ በታደጊዎች ስነልቦና ላይ የሚያሳድረው ጫና
ቀላል አለመሆኑና በተዛማጅ ጥናት ላይ የተዳሰሱ ጥናቶች ከስነቃል፣ ከሀገረሰባዊ ዕምነት
ትዕምርትነት አንፃር ያልዳሰሱትን ጉዳዮች ወይም ክፍተቶች ለመሙላት የሚያስችሉ
ነጥቦችን አመላክቷል፡፡