Abstract:
ይህ ጥናታዊ ጽሁፍ የቁባ ኣባ አረቡ የመውሊድ ክብረ በአል ስርዓተ ክዋኔ ሂደት ትንተና ላይ ትኩረት ያደረገ
ሲሆን፤ የጥናቱ ዋና ዓላማ የቁባ አባ አረቡ የመውሊድ በአል ስርአተ-ከበራ (ከዚያራ እስከ ፍጻሜው) ያለውን ሂደት
መተንተን ነው፡፡ አላማውን ለማሳካት ጥናቱ በገላጭ የምርምር ስልት በመመርኮዝ የተከናወነ ሲሆን፤ ያነሳቸው
የምርምር ጥያቄዎችም (1) የቁባ አባ አረቡ የመውሊድ ስርዓተ ክዋኔ ምን ይመስላል? (2) በመውሊድ ስርዓተ
ክዋኔው ላይ የሚቀርቡት ቃላዊ ግጥሞች ክዋኔ እና ክብረ በዓሉን አጅበው የገቡ ቁሳዊ ባህሎች ከሐይማኖታዊ
ገጽታቸው ባሻገር ምን አይነት ፎክሎራዊ ገጽታ አላቸው? የሚሉ ጥያቄዎች በጥናቱ ለመመለስ ተሞክሮዋል፡፡ አላማ
ተኮርና የጓድ ጠቆም የንሞና ዘዴን በመጠቀም የጥናቱ አካባቢና ናሙናዎች ምርጫ የተከናወነ ሲሆን፤ ለጥናቱ
አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በምልከታ፣ ቃለ መጠይቅ እና በተተኳሪ የቡድን ውይይት በመሰብሰብ በአውዳዊ ወይም
ክዋኔ ተኮር ንድፈ ሀሳብ የተደገፈ ትንተናና ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ በጥናቱ ግኝቶች መሰረት፤ የመውሊድ በአሉ ክዋኔ
የየራሳቸው ዓላማ ያላቸው ሁነቶች ድምር ውጤት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከጥናቱም የተገኘው ውጤት የቁባ
አባ አረቡ የመውሊድ ክብረ በዓል ከዋናው ዋዜማ በፊት በወንዶችና ሴቶች መውሊድ ስርአተ ክዋኔዎች የሚጀምር
ሲሆን ዋናው የዋዜማ ቀን ደግሞ ረቢያል አወል 11 ሌሊት ለ12 መንጊያ ነው፡፡ በመውሊድ በአሉ የአከባበር ስርዓት
ላይ የተስተዋሉት የክዋኔ ሁነቶች ዚያራ፣ ዱአ (ምርቃት)ና መንዙማ ናቸው፡፡ የነዚህ ሁነቶች አጠቃላይ መጠሪያ
‹‹ዱአይ›› እንደሚባልና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ሁነቶች በስፋት የተንጸባረቁበት እንደሆነ ጥናቱ
ቃኝቷል፡፡ ከዚሁ ጎን የታዩት የመንዙማ ግጥሞች በተከወኑበት የክዋኔ ሒደት አንጻር በሁለት መንገድ (በድቤ እና
በእንጉርጉሮ) እንደሚባሉ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን፤ የመውሊድ ስርዓተ ክዋኔን አጅበው የገቡትን ቁሳዊ ባህሎች
ከአሰራራቸውና ጠቀሜተቸው አንጻር በሶስት መልኮች (ቃላዊ ግጥሞቹን አጅበው የሚገቡ፣ የመመገቢያና ጌጣጌጥ)
እንደሚፈረጁ ጥናቱ ተመልክቷል፡፡ እነዚህን ቁሶች ማህበራዊ፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ጉዳይ ጋር ግንኙነት ያላቸውና
የተፈጥሯዊና ተለጣፊ እሴት፣ ታሪክ ነቃሽነት፣ ተወካይነትና ውስንነት ሆነው ገጽታ እንዳላቸው ጥናቱ ቃኝቷል፡፡ የቁባ
ኣባ አረቡ የመውሊድ ክብረበአል ተግባርም የማጠናከር፣ የማምለጥና ማህበረሰቡን የመቆጣጠር ተግባር ያለው ከመሆኑ
አንጻር ይህ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊና ቁሳዊ ባህል ማህበረሰቡን ከማስተዋቅ አንጻር ያለው ፋይዳ ቀላል ባለመሆኑ ጥበቃ
ቢደረግለት የሚል አስተያየት ተሰጥቷል፡፡