Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና አላማ የተማሪዎች የማዳመጥ ብልሀት አጠቃቀም ከአዳምጦ መረዳት ችሎታቸው ጋር ያለውን ተዛምዶ መመርመር ነበር፡፡ ጥናቱ ተዛምዷዊ ንድፍን የተከተለ ሲሆን ስታስቲካዊ ገላጭ የምርምር ስልትን ተከትሎ የቀረበ ነው፡፡ የጥናቱን ተሳታፊዎች ለመምረጥም እድል ሰጭ ናሙናን መሰረት በማድረግ በረድፋዊ ንሞናን በመጠቀም ተመርጠዋል፡፡ ተሳታፊዎቹም በሙጃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ 2013 ዓ.ም በአስርኛ ክፍል የሚማሩ 154 ተማሪዎች ናቸው፡፡ መረጃውም የማዳመጥ ብልሀት መለኪያ በፅሁፍ መጠይቅና በአዳምጦ መረዳት የችሎታ መለኪያ ፈተና ተሰብስበዋል፡፡ መረጃዎቹም መጠናዊ የምርምር ዘዴን በመጠቀም በ(SPSS 20) ኮምፒውተር ሶፍት ዌር በፒርሰን የተዛምዶ ተሰልተው በገላጭና ድምዳሜያዊ ስታትስቲክስ ተተንትነዋል፡፡ በፅሁፍ መጠይቅ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት የተማሪዎች የብልሃት አጠቃቀም በጥቅል የብልሃት አይነት 75 (50%) አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀሙና ሁልጊዜ የሚጠቀሙ ሆነው ሲመዘገቡ 41 (27.33%) ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የማይጠቀሙና በጭራሽ የማይጠቀሙ ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ ከብልሃት አይነቶች መካከል የበለጠ የሚጠቀሙት አእምሯዊ ብልሃት ሲሆን ይህም በፅሁፍ መጠይቅ በተገኘው መረጃመሰረት ከፍተኛ ተጠቃሚ (M= 3.85, SD=1.15) በሆነ ውጤት ከሁለቱ የብልሃት አይነት ቀዳሚ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በማዳመጥ ብልሃት አጠቃቀምና በአዳምጦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በተመለከተ አጠቃላይ (r=.523) ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በመሆኑም በተማሪዎች በማዳመጥ ብልሃት አጠቃቀምና በአዳምጦ መረዳት መካከል አዎንታዊና ጉልህ የሆነ ተዛምዶ እንዳለው በስታትስቲክስ ጉልህ ልዩነት (p<0.05) ታይቷል፡፡ ስለዚህ የአማርኛ ቋንቋ መምህራን የማዳመጥ ብልሃትን መጠቀም አዳምጦ የመረዳት ችሎታን ለማጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በመገንዘብ ማዳመጥን በክፍል ውስጥ በሚያስተምሩበት ጊዜ ተማሪዎች ብልሃትን እንዲጠቀሙ ቢደረግ፣ የአማርኛ ቋንቋ መምህራን ማዳመጥን በሚያስተምሩበት ጊዜ የተማሪዎችን የብልሃት አጠቃቀም ያማከለ ቢሆን፣ የመማሪያ መጽሐፍት በተለይም ደግሞ በማዳመጥ ተግባር ላይ ያሉ መመሪያዎችና ትዕዛዛት የማዳመጥ ብልሃትን የሚያስጠቅሙ ሆነው ቢዘጋጁ የሚሉ ለተማሪዎች አዳምጦ የመረዳት ችሎታ እድገት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑ በቀጣይ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪና ሰፊ ጥናት ቢካሄድ የተሻለ ግንዛቤ ሊገኝ ይችላል፡፡ የሚሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ተጠቁመዋል፡፡