Abstract:
የዚህ ጥናት አብይ ዓላማ በኦሮምኛ ቋንቋ አፋቸውን የፈቱ የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የቡድን ሥራን በመጠቀም ቃላዊ ተግባቦትን በማስተማር የቃላዊ ተግባቦት ብቃታቸውን ለማዳበር ያለውን አስተዋጽኦ በከፊል ፍትነታዊ ምርምር መፈተሸ ነበር፡፡ ይህን ዓላማ ለማሳካትም በጭንጊ የሚገኘው የጭንጊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአመቺ ናሙና ተመርጧል፡፡ በትምህርት ቤቱ ከሚገኙት ስድስት የአስረኛ ክፍል የመማሪያ ክፍሎች የአንዱን ክፍል ተማሪዎች ለሁለት በመክፈል በቀላል የእጣ ናሙና ተመርጠዋል፡፡ በመሆኑም የሙከራው ቡድን ተማሪዎች በቡድን ሥራ እየታገዙ ቃላዊ ተግባቦትን ሲማሩ፣ የቁጥጥር ቡድኑ ተማሪዎች ደግሞ በተለመደው የቃላዊ ተግባቦት ትምህርት አቀራረብ የቃላዊ ተግባቦት ትምህርትን በስድስት ሳምንታት ለ12 ክፍለ ጊዜያት እንዲማሩ ተደርጓል፡፡ መረጃዎቹ በቃላዊ ተግባቦት ብቃት ፈተና በቅድመትምህርት እና በድህረትምህርት ተሰብስበዋል፡፡ በቃላዊ ተግባቦት ፈተና የተሰበሰበው መረጃ በየአይነት ከተደራጀ በኋላ በገላጭና በድምዳሜያዊ ስታትስቲክስ (የነጻ ናሙናዎች ቲ-ቴስት) ተተንትንዋል፡፡ በውጤት ትንተናው መሰረትም የሙከራው ቡድን ድህረትምህርት የቃላዊ ተግባቦት ብቃት ፈተና አማካይ ውጤት(16.63) ከቁጥጥሩ ቡድኑ የቃላዊ ተግባቦት ብቃት ፈተና አማካይ ውጤት(13.60) በልጦ ጉልህ ልዩነት (p=0.000) አሳይቷል፡፡ ከጥናቱ ግኝት በመነሳትም በቡድን ሥራ ቃላዊ ተግባቦትን ማስተማር የተማሪዎችን የቃላዊ ተግባቦት ብቃት ለማሳደግ ከተለመደው የቃላዊ ተግባቦት ማስተማሪያ ዘዴ የበለጠ አስተዋጽኦ አለው ከሚል መደምደሚያ ላይ ተደርሷል፡፡ ስለዚህም የተማሪዎችን የአማርኛ ቋንቋ ቃላዊ ተግባቦትን ለማዳበር በቃላዊ ተግባቦት የማስተማር ዘዴዎች ውስጥ ተማሪዎች እራሳቸውን ችለው መማር እንዲችሉ የቡድን ሥራን በመጠቀም በማስተማር የተማሪዎችን ቃላዊ ተግባቦት ብቃታቸውን የሚሻሻልበትን ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል፡፡