Abstract:
በዚህ ጥናት በደቡብ ክልል ስራ ላይ ባሉ በ5ኛና 6ኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት ዉስጥ የተካተቱ የሰዋስዉ ትምህርት ይዘቶች አቀራረብና አደረጃጀት ምን እንደሚመስል ተገምግሟል፡፡የጥናቱን ዓላማ ለማሳካት ገላጭ የምርምር ንድፍ የተመረጠ ሲሆን የተገኙት መረጃዎች በዓይነታዊ የምርምር ዘዴዎች ተተንትነዋል፡፡በጥናቱ ሰነድ ፍተሻና ቃለመጠይቅ ጥቅም ላይ የዋሉ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች ናቸዉ፡፡ጥናቱን ለማካሄድ በተተኳሪዎቹ መማሪያ መጻሕፍት ዉስጥ የተካተቱ የሰዋስዉ ትምህርት ይዘቶችን ለይቶ በማዉጣት በክለሳ ድርሳን ክፍል የቀረቡትን Larsen Freeman(1991)፣ Harmer(1991) እና Ur(1996)የሚያራምዷቸዉን ንድፈ ሀሳባዊ መሰረቶችን በመመርኮዝ ትንተና ተሰጥቶባቸዋል፡፡በጥናቱ የተገኘዉ ዉጤት እንደሚያመለክተዉ የይዘቶች አቀራረብን በተመለከተ በታላሚዎቹ መማሪያ መጻሕፍት ዉስጥ ከአጠቃላይ ወደ ዝርዝር የአቀራረብ ስልት ያልተካተተ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ዉጤት ተኮር በሆነ ስልት የቀረቡት ይዘቶች ሂደት ተኮር በሆነ ስልት ከቀረቡት ይዘቶች አብላጫዉን እንደሚይዙ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ከአደረጃጀት አንጻር ደግሞ አብዛኛዎቹ ሰዋስዋዊ መልመጃዎች በተለያዩ ምዕራፎች እየተደጋገሙ መቅረባቸዉን ጥናቱ አሳይቷል፡፡ነገር ግን በርካታ ይዘቶች ስፋትና ጥልቀታቸዉን ሳይጨምሩ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ተደራጅተዉ መቅረባቸዉን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ይሁን እንጂ በተተኳሪዎቹ መጻሕፍት ዉስጥ የተካተቱት የሰዋስዉ ትምህርት ይዘቶች ከሰዋስዉ ትምህርት ይዘቶች አቀራረብና አደረጃጀት መርሆዎች አኳያ ሲፈተሹ ሰዋስዋዊ ይዘቶቹ በምሳሌዎች እየታገዙ መቅረባቸዉና በተለያዩ ምዕራፎችና ክፍሎች እየተከታተሉ መደራጀታቸዉ ከጠንካራ ጎናቸዉ መካከል የሚጠቀስ ሲሆን አብዛኛዎቹ ይዘቶች ደግሞ ጥልቀታቸዉን ሳይጨምሩ መደራጀታቸዉ እንደ ደካማ ጎን ታይተዋል፡፡ በመሆኑም የታዩት ደካማ ጎኖች ወደፊት መጻሕፍቱ በሚሻሻሉበት ወቅት እንዳይደገሙና ጥንቃቄ እንዲደረግ አጥኝዋ ለመጠቆም ትወዳለች፡፡