Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና አላማ በ2007 ዓ.ም በታተመው የ5ኛ ክፍል የአማርኛ መማሪያ መጽሐፍ ውስጥ የቀረቡ የአንብቦ መረዳት መልመጃዎች አዘገጃጀትና የክፍል ውስጥ አተገባበር ፍተሻ ነው፡፡ ጥናቱ ገላጭ የምርምር ንድፍን የተከተለ ሲሆን በሰነድ ፍተሻና በቃለ መጠይቅ መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ በጥናቱ አስፈላጊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ አምስት መምህራን በጠቅላይ የንሞና ዘዴ ተመርጠው ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል፡፡ የተሰበሰበው መረጃ በአግባቡ ተደራጅቶ ትንተና ተደርጎበታል፡፡ ከመረጃዎቹ የተገኙት ውጤቶች የሚያመለክቱት የአንብቦ የመረዳት መልመጃዎች የይዘት አቀራረብ ለመማር ማስተማሩ ሂደትም ሆነ ለተማሪዎቹ ልምምድ አመቺ መሆናቸውን፤ አንብቦ የመረዳት መልመጃዎች የመጽሐፍ አቀራረብ ተገቢነት፣ የተማሪዎችን ደረጃ፣ ዕድሜና ችሎታ እንዲሁም ዳራዊ እውቀታቸውን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ መሆናቸውን፤ የመማሪያ መጽሐፉ አንብቦ የመረዳት መልመጃዎች በተቀናጀ መልኩ እንደተዘጋጁና የማስተማሪያ መሳሪያዎቹ አንብቦ የመረዳት ክሂሎችን ለማስተማር እገዛ እንዳላቸው የጥናቱ ውጤት ያመለክታል፡፡ በአንጻሩ የአንብቦ መረዳት መልመጃዎች አቀራረብ ለትምህርቱ ከተመደበው ሰዓት ጋር ያለመጣጣም ችግሮች መኖራቸውን፣ አልፎ አልፎ ስለ መልመጃዎቹ አሰራር ሙሉ መረጃ የማይሰጡ መመሪያዎች በመጽሐፉ ውስጥ መካተታቸውን የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡