Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና ትኩረት የአፋን ኦሮሞ አፈ-ፈት ተማሪዎች አማርኛን በሁለተኛ ቋንቋነት ለመማር ያላቸውን ተነሳሽነትና የትምህርት ውጤት ተዛምዶ መፈተሸ ነው፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በኢሉባቦር ዞን በሁሩሙ ወረዳ ሁሩሙ ሁለተኛ ደረጃና በሶንጣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2013 ዓ.ም በመማር ላይ በሚገኙት 110 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ነው፡፡ በዕድል ሰጪ የናሙና አመራራጥ ዘዴ ከተመረጡት ተማሪዎች በጽሑፍ መጠይቅና በፈተና የጥናቱ መረጃዎች ተሰብሰበዋል፡፡ በገላጭ ስታቲሲቲክሶችም ተተንትኖ የተብራራ ሲሆን በመረጃው ትንተና መሠረት በተማሪዎቹ አማርኛን በሁለተኛ ቋንቋነት የመማር ተነሳሽነትና በቋንቋው ትምህርት ውጤት መካካል የጎላ ተዛምዶ አልታየም፡፡ በተነሳሽነት አይነቶችና በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ውጤት መካከልም ተዛምዶ አልታየም፡፡ ይሁን እንጂ በሁለተኛ ቋንቋ (አማርኛ) የመማር ተነሳሽነት በፆታ መካከል ተዛምዶ ታይቷል፡፡ የሁለተኛ ቋንቋ ተነሳሽነት በትህምርት ቤትና በትምህርት ቤት መካከልም የውጤት ልዩነት አሳይቷል፡፡ ከጥናቱ ውጤት በመነሳት ሁለተኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራን ትምህርቱን ሲያቀርቡ የተማሪዎችን ፍላጎትና ስሜት በሚያነሳሳ መልኩ ቢያቀርቡ፣ ሴቶችም ሆነ ወንዶች ተማሪዎች ምን አይነት ማበረታቻ ቢደረግላቸው ውጤታማ እንደሚሆኑ አስቀድሞ በማወቅ የተማሪዎችን የመማር ተነሳሽነት ለማጠናከር የሚረዱ ተግባራትን ቢያከናውኑና ይህንኑ መሠረት ያደረገ ድጋፍና ክትትል ቢያደርጉ የተማሪዎቹ የሁለተኛ ቋንቋ ትምህርት (አማርኛ ቋንቋ ትምህርት) ተነሳሽነት ሊሻሻል ይችላል የሚሉ የመፍትሔ ሀሳቦች ተጠቁመዋል፡፡