Abstract:
ይህ ጥናት በደብረ ምጥማቅ ሸንኮራ ቅዱስ ዮሀንስ ገዳም የሚነገሩ ተረኮች ስነምግባር ከማስተማር አንፃር ያላቸውን ፋይዳ መፈተሸ በሚል ዋና አላማ የቀረበ ነው፡፡ ይህ ጥንታዊ ገዳም ከተመሰረተ 394 አመታትን ያስቆጠረ ትልቅ ገዳም ነው፡፡ በዚህ ጥናት አስራ አንድ መረጃ አቀባዮች የተሳተፉ ሲሆን ስድስቱ ቁልፍ መረጃ አቀባዮች ናቸው፡፡ የጥናቱ ዓላማም የተሳካ ይሆን ዘንድ ጽሁፋዊ ማስረጃዎችን ከመጠቀም በተጨማሪ በቃለ መጠይቅ፣ በሰነድ ፍተሻ፣ በቡድን ተኮር ውይይት መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ የተሰበሰቡ መረጃዎችም በማስታወሻ፣ በምስል፣ በመቅረጸ ድምጽ እና እንደአስፈላጊነቱ በቪደዮ ካሜራ በማጠናቀር መረጃዎቹን ክግብ ለማድረስ ተሞክሯል፡፡ እነዚህ ተረኮች በገላጭ የምርምር ዘዴ በመጠቀም እና በተረክ ትንተና ንድፍ ሃሳብ መንደርደሪያነት ለመተንተን ተሞክሯል፡፡ እንዲሁም የተጠኝ አካባቢና የማህበረሰቡ ዳራዊ ገለጻ ተቃኝቷል፡፡ በጥናቱ የተለያዩ ተረኮች የተሰበሰቡ ሲሆን ተረኮቹ የገዳሙን ማህበረሰብ ስነምግባር በማስተማር እና በመቆጣጠር ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ለማየት ተችሏል፡፡